Sunday, May 15, 2016

ብርሃን ናፋቂዎች

          
የጨለመ ጨልሞ አይቀር ይነጋል ብለው ቢያወሩ
ሌቱን ለማንጋት ብለው ስንቶች ሲገፉ አደሩ
የንጋት ወጋገን ናፍቋቸው እድሜ ህይወታቸውን ገበሩ፡፡
“ብርሀን ከሩቅ አይተናል” ያሉም ሰባ ሰገሎች
መንጋውን ተከተል ብለው ከግመል ወጡ ጥቂቶች
ጨልሞ አይቀር የተባለን ሌቱንም ለመግፊያ ብለው
ጥቂቶች ከግመል ያሉ መንጋውን በተራ ማግደው
ከግመላቸው ጋራ ይሞቃሉ እሳት ከበው::
ይህ ጨለማን ገፊ መንጋ ነገን ሊያይ ተስፋ የጣለ
በዛሬ ድቅድቅ መሆን ውስጥ በነገ ተስፋ ያመነ
በዘመን መፈራረቅ ውስጥ ጨለማን ሲገፋ ኖረ::
የሰባ ሰገሉን ምሪት የጥበበኞቹን መንገድ
አናምንም ብለው የካዱ
ብርሀናቸውን ፍለጋ በአሸዋው ባህር ነጎዱ
እኒ የብርሀና ሕይወት ተስፈኞች
ግብዓታቸውን በባህር ወስብሀት ብለው ያሉ
ነገ ብርሀን ሊሆን በነፍስያቸው ያምናሉ
ለሰባ ሰገሉ የታመኑ እናንተው ትመሩን ብለው
ሌቱን ሊገፉ የጣሩ
በውድቅት ተኩላ በልቷቸው በደም ርሰው አደሩ
ባለ ግመሉን የናቁ
ተኩሎች መንጋ ነጠቁ
ጨቅሎችን ከእናት አራቁ
በመንጋው መበታተን ውስጥ ክፉዎች ደማቅ ሳቅ ሳቁ 
መንጋው ይነጋል ብሎ ሰባ ሰገሉን አምኖ
ጨለማን እገፋ ብሎ የነገን ብርሀን ናፍቆ
ሲገፋ ሲገፋ ያድራል አንጀቱን ከሆዱ አጣብቆ
ቀና ሲል ሰማይ ይሸሻል
ቢያንጋጥጥ ከርሱ እንባ በቀር
ጠብ የሚል ከሰማይ ጠፍቷል
ተኩላ ልጁን ይነጥቃል
ባህር ልጁን ይወስዳል
ይህም ሁሉ እየሆን ሰባሰገሉን ያሞቃል
መንጋው
ጨለማን እገፋ ብሎ
ብርሀን አገኘው ብሎ
ተስፋውን በተስፋ ጥሎ
ይገፋል
ይገፋል
ወይ ያልፋል
ወይ ያልፋል፡፡
  
                                      ኤልያስ ታ.
                                      04 18 16
         ስጋችንን የለመደው ሜዲትራንያን ዛሬም ብዙዎቼን በወሰደ ግዜና ጋምቤላ ያሉ ሁሉ በፅልመት በተሸፈኑ ግዜ ተፃፈ፡፡


No comments:

Post a Comment