የማስንቆ ዜማ
ደምቆ ከተሰማ
ይልኻል ተቀበል
የቅኔውን ማዕበል
“ሀገሬ ዜማነሽ ሀገሬ ውብ ቅኔ
ያዜሙሽ ይዘርፉሽ የበዛልሽ ፍሬ”
ይላል ባለስንኝ ሞጋች ሀሳብ ያለው
ተቀባይ ካገኘ ድምጡን ከፍ ያረገው
የማስንቆ ጅማት በዜማ ሲዋዛ
የባለቅኔ ቃል ከሀሳብ ሲነሳ
ይልኻል ተቀበል ተቀበል ጨዋታ
እየሳቀ ሚያለቅስ የኑሮ እውነታ::
እዚም ጨዋታ አለ
በማስንቆ ያይደለ
በጭብጫቦ ያይደለ
ዜማ ያልታደለ
እዚም ጨዋታ አለ
ተቀበል ይልኻል
ከዘማኞች መንደር
በነ ፈስብክ ሀገር
እውቀትና ስድብ የተሰናሰኑ
በቧልትና እውነት እጣን የታጠኑ
ለፌዝና ስድብ ተማርኮ የተረታ
እዚ አለ ጨዋታ https://youtu.be/jzRA5IEj_qY
ይኸው እዚኛው ጥግ
ከመፅሀፍ ርዕስ የተገኘ እውቀት
በአሉባልታ ወሬ የታፈነ ግምት
ተቀበል ይልኻል የማወቁን ልኬት
ደግሞ በዚኛው ጫፍ ከሀይማኖት ግድግዳ
ከኔ እበልጥ እኔ እኔ በልጥ የአማኞች ሽኩቻ
ቅዱስ ቃል ከስድብ ከቧልት ተዳምሮ
ላጥምቅህ ይልኻል ከሀይማኖት ጏሮ
ተቀበል እዚ ጋር
የፖለቲካን ጥግ የሀገርን ችግር ተንታኝ ዲስኩረኛ
የመንግስትን ችግር ፈትፋች ታምረኛ
ተቀበል ይልኻል መፍትሄ ለሀገር
ለምስኪኑ ወገን፡፡
መሰንቆ ባትሰማ
ባይኖረውም ዜማ
ተቀበል ይህንን ጀግንነት
ሁሉን አዋቂነት
ሁሉን ሰዳቢነት
ሁሉን ተንታኝነት
ተቀበል
ሀገር ሲቃጠል ሰልፊ
ደገፍ ብለ- ብትነሳ
የሚወድልክ እልፍ ነው
ለላይክ እጁ ማይሳሳ
መታደል እኮ ነው እናንተው
ስንት ደራሲ --- ስንት ሀያሲ
ስንት ገጣሚ --- ስንት አራሚ
ስንት ለጣፊ--- ስንት ጠሀፊ
ስንት ጀግና የጦር መሪ
ድንበር አፍራሽ ድንበር ሰሪ
ባለ ብዙ ግብረ ብዙ
ሀሳብ ብዙ ስድበ ብዙ
ጠብ ደሞዙ
የዘመነ ባለ ዜማው
ቅኝተ ብዙ ፌስቡከኛው
ይልኻል ተቀበለኝ
ሀገርን በላይክ ብዛት በኮመንት ሊተምንልኝ
ተቀበል፡፡
ኤልያስ ታ.
04/28/2016

No comments:
Post a Comment