Sunday, February 14, 2016

አንድ ማኪያቶ


------------------
ውዴ እዛች ካፌ

ፈገግታ የማታውቅ የቤቱ አሳላፊ

ምን ልታዘዝ ያለች ትሪ ይዛ ሰፊ

አንድ ማኪያቶ ከአንድ ጣፋጭ ኬክ ጋር

ቡና እንደወረደ ያልገባበት ስኳር

ይዛ የተመለሰች

አውግተን አውግተን  ከጨረስን ነበር፡፡

ትኩስ ማኪያቶ ቡና ያልበዛበት ወተቱ ያላነሰ

ውበቱ የሚማርክ ለአይን ያልደፈረሰ

ከግራ ወደቀኝ ታማስይው ነበር

ከጨመርሽው ስኳር፡፡

ፈገግታ የማታውቅ ያቺ አሳላፊ

ማንኪያ ታመጣለች ማንኪያ እየወሰደች

ላንቺ ፈገግ ብላ እኔን ገላመጠች

.….ይህ ...ትኩስ ማኪያቶ

ወተቱ ከቡናው ቡናው ከወተቱ የተሰናሰለ

ከውስጡ አንደኛውን ማውጣት ማነው የቻለ?

ቡናውን ከወተት ማነው የነጠለ?

አየሽ ከግራ ወደቀኝ ከላይም ወደታች

በማንኪያ ቢማሰል

ይዋሀዳል እንጂ ከቶም አይነጠል፡፡



አየሽው ባሬስታው የማሽኑ ጌታ

ይህ ባለችሎታ

ማኪያቶ ቢሉሽ ማኪያቶ ነው  ከልቡ ሚሰራ

ወተቱን ከቡና ቡናውን ከወተት ያኖረ በጋራ

ይህም የኛ ዓለም ነው

የማሽኑ ጌታ እርሱ ከሰማይ ነው

እኔ ያንቺ ቡና አንቺ የኔ ወተት

እርሱ የሰራውን ይህን ማኪያቶ አይለየውም ዘበት

አየሽው ባሬስታው አየሽው ጥበቡን

ምን ማንኪያ ቢበዛ አማሳይ መሀሉን

ሊለየው እንዳይችል ቡናና ወተቱን

ድንቅ አድርጎ ነው መጥኖ ያዋሀደ

ባሬስታው እርሱ ነው ሁሉን የፈቀደ፡፡



                ኤልያስ.ታ
                             02/14/2016
                                       EK

No comments:

Post a Comment