Wednesday, July 22, 2015

ተንስዑ

ካለውበት ስፍራ የብረት ቅልጭታ እጅግ ከበዛበት
ግርግር ሁካታ ጎልቶ ከሞላበት
ይሰማኛል ዜማ የመቅደሱ ደውል
የካህኑን ፍታት ተከትሎ አሜን ሲል
ይሰማኛል ወገን በተመስጦ ሆኖ
ከደኙ ሲማጠን በፈጣሪው አምኖ
ይሰማኛል ከዚ ከጫጫታው መሀል
ተንስዑ የሚለው
ስገዱ የሚለው
                     የዲያቆኑ ቃጭል
ዲያቆኑ ለጥቋል
ወደ ምስራቅ እዩ ተመልከቱ ወደዛ
ይላል መሀል ቆሞ በእጣኑ መዓዛ
ከምዕራብ ያለው ከምስራቅ ርቄ
እኔ ከዚ ያለው ለዓለም ወድቄ
                      ዓለምን ናፍቄ
የምስራቁን ጥሪ የዲያቆኑን ዜማ
                       ለነፍስ የተስማማ
በናፈቀ ልቤ ባህር አሻግሬ
                 ተራራ አሳብሬ
የምስራቋን ሀገር ቅዳሴ አደምጣለው
የእጣን መዓዛን በማያውቅ አየር ውስጥ እጣን አሸታለው
ጉልበቴን በሀሳብ ከደጁ ሰድጄ ጌታ ሆይ እላለለው
እላለው እላለው እላለው እላለው።

              ኤልያስ .ታ
               07/22/2015

Thursday, July 9, 2015

የአርምሞ ቃላቶች

የአርምሞ ቃላቶች
----------------------
የባለ ቅኔው ጉልበቱ
የቃላት ውበት ፍሰቱ
ለሌላ ከሆነ እንጂ
አልበጀም አልሆነም ላንቺ
እንዲ ልኬት የማይሰጡት
ቃላት መርጠው ማይፈርጁት
ዜማ ደርሰው ማይዜሙት
ከመገለጥ በላይ ያለ
ከመወደስ ልቆ ያለ
ምን ይሉት ፍቅር ነው አንቺው አፍን በእጅ ያስከደነ
ቀልብን ሰርቆ የጠፋ ልብ ላይ ነግሶ የገነነ።
                /////////
ይህስ ቃል ከየት ነው የመጣ ፍቅርሽን ሊገልጥ የጣረ
ላይሆንለት ሚደክም አብዝቶ እንዲ የታተረ
አንድ ዘራፊ ይጥፋ ቅኔን በዜማ `ሚያሳምር
እማ ፍቅርሽን ገልጦ ብእሩን ላንቺ ሚሰድር
ነው ወይስ እናት ዜማ ነች ተደምጣ የማታበቃ?
እናት ቅኔ ነች ተፈታ የማታበቃ?
ነኝ
ለሷ መግለጫ ያጣው ፍቅሯን እንዲ ለማለት
አፌን በእጄ ከድኜ በአርምሞ የምቀኛት
እንዲህ ነው
አረምሟዊ ነው ዜማዬ ቅኔዬ ቃልም የለውም
ፍቅሯን በማይገልጥ ውዳሴ መውደዷን አላረክሰውም
ከመገለጥ በላይ ነው የሷ ከመተርጎም የላቀ
መውደዷን መቀበል እንጂ ለመግለጥስ የረቀቀ
እሷን መኖሩ ይበጃል በአርምሞ ውስጥ ተውጦ
እሷን ለማመስገኛ ቃላቱስ ከወዴት መጦ?
                 !!!!!!!
እንዲ ብቻ ልበልሽ እማ እኖርሻለው
አንቺን ለመግለጥ ቃል ብመርጥ ፍቅርሽን አሳንሳለው
በቃ እማ     ..........

በቃ።
                                 ኤ.ታ
                                May 2015
    

የከረረ ክራር

የከረረ ክራር
ታም…. ታራራራም…. ታራራም
ታራራራራም
ራምራምራም 
እራምራምራም
ይላል ያስናቁ ክራር
ጣቶቿ ጅማቱን ሲያከር
ስትገርፈው ቅኝት ቀይራ
ይላል ታራራራራራራራም ታራራም
አላወቀች እሷትዝታን ስትቃኝ
ክራሯን ስትገርፈው
አንጀቴን በጣቷ እንደነዘረችው
በትዝታ ይዛ ከዚ እዛ ማዶ እንዳሻገረችው
ታምራራራራም ራራም ራም እያለ ወደዛ
ከፍቅሬ መዓዛ
ከእቅፉ በታች ከመውደዷ ጋራ
ልቤን በልቧ አስራ
ትለኛለች ውዴ
            ውዴ የኔ ፍቅር
ከጎንክ እንደዋልኩ ከእቅፍህ ልደር?
ትለኛለች ነፍሴ
የሌት መወድሴ
የቀን መናፈቄ
በአስናቁ ክራር ተስላ ከፊቴ
ታምታራም ታራራም ታራራም ታረረረረም ራም ራምራምምም
የሚገረፍ ክራር የሚያለቅስ አንጀት
አንቺን ያሰበ ለት
ታራራም እያለ ትዝታሽን ይዞ
የተጕዝነው ጉዞ
በፍቅርሽ በናፍቆት የሰለለ ልቤ
እያለ ሚያዜም የሌት ቀን ርሀቤ
ዜማውን ያወርዳል ተቀበይ ትዝታ
የአስናቁን ክራር የአደመጥሽው ለታ
ርም ርም ርምርምርምርም
ማራኪ ፈገግታሽ ይኸው ፊቴ ግጥም
እኔ ደግሞ ግጥም ሥገጥም ሥገጥም
የሰማች አስናቁ ክራሯን አነሳች
ዜማዋን ለጠቀች
“አልሻም ማስንቆን የፈረስ ጭራ ነው
አልሻም ዋሽንትን ወንዝ ዳር በቃይ ነው
አምጡልኝ ክራሬን አንጀትን በአንጀት ነው”
አለች ክራሯን ገረፈች
አንጀቴን ገረፈች
አንቺን የናፈቀ ነፍሴን እህ አስባለች
ክራሩ ከረረ ናፍቆቴ ከረረ
ይህንን የሰማ ክራር ተናገረ
አንቺን የናፈቀ
በናፍቆት አለቀ፡፡
                        ኤልያስ ታ.
                        06/25/2015