Thursday, February 9, 2017

የተወጠረ እንባ


በሰዓሊ ሸራ ተወጥሮ ሚታይ የቆንጆ ልጅ እንባ
ሸራውን ያራሰ
ቀለም የጨረሰ ሀዘኗ ሚጋባ
ይታየኛል ለቅሶ
 ከግድግዳው መሀል በቀለም ርሶ።
የዚችን ውብ ልጅ ገፅ እንዲህ ያጨለመ
ያማሩ ዓይኖቿን በእንባ ያደከመ
ምን ያለ ሰዓሊ ምን ያለ ቀቢ ነው
እንዴት ብትፈትነው እንዴት ቢጣላት ነው?
መሳም የሚጎዳው የመሰለ ጉንጯ በእንባ ይታጠባል
ሰዓሊው ወይ በሀዘን ወይ በደስታ ሆኖ ቀለም ይጨርሳል
ይህን የሚታዘብ ምስኪን እድምተኛ
በሰዓሊ ብሩሽ ለሆነ መናኛ
ለሚፈስ እልፍ እንባ ቆሞ ይተክዛል
ይህ ማራኪ ውበት ከማንባቱ በፊት እንደምን ይመስላል
እንደው ስቆ ያውቃል
ብሎ ይጠይቃል?

ሰዓሊ አሁን ሳቀ
የማያቀውን ፊት ለማወቅ ናፈቀ
ስቆ ማያቅን ፊት በሳቅ አጠየቀ
ሊያስቃት የሚችል
ሊያስነባት የሚችል
ህይወቷን በብሩሽ ቆርጦ የሚቀጥል
ሰዓሊ ናፈቀ
ስቆ ማያቅ ፊቷን በሳቅ ውስጥ ፈለገ
ትስቅ ይሆን እሷ
እንባዋስ ይቆማል
ሰዓሊ እጅግ ጓጉቷል
ምስኪን እድምተኛ ወደላይ አንጋጧል
መሳል ተጀመረ........


ኤታ
02/09/2017