Monday, March 23, 2015

መንገድተኛ ልጅሽ

መንገድተኛ ልጅሽ

ቀኝ አውለኝ ብሎ በናት ባባት ጠሎት ከቤቱ የወጣ
ምስኪኑ ወዳጄ መንገድ ግራ አጋብቶት ቀረ እንደወጣ
ይህ ምስኪን ወንድሜ በሀገሩ በቀዬው ስንቱን መንገድ መርቶ
መንገድ ለጠፋቸው መንገዱን አብርቶ
ስንቱን እንዳልሸኘ
ዛሬ በሰው ሀገር  በመንገድ ተሞኘ
 ይህ መንገድ አዋቂ
እግር አስታራቂ
ቢጠፉ ወዴት ባይ
ቢስቱ አለው ባይ
ዛሬ በሰው ሀገር ሰኔው ከሰኞ ጋር አብረው ቢያብሩበት
ወጦ አልተመለሰም መሄጃው ጠፋበት!!
… ሰማሽ አንቺ ምስኪን እናት አንቺ ምስኪን ሀገር
ልጅሽ መንገድ ገብቶ እንደወጣ ሲቀር
ያ ከጋራ ሸንተረር ቀበሌ አቋርጦ
ወረዳን አሳብሮ
ካሻው መንደር ዘልቆ
ካሻው ቀዬ አድሮ
ወዳሻው የሚበር
ያ ደፋሩ ልጅሽ ጠፋብሽ አንቺ ሀገር!!
…ሲናገር ኩራቱ ግርማ ሞገስ ያለው
ምስኪኑ ወንድሜ ዛሬ በሰው ሀገር እሱ ሌላ ሰው ነው!!
..ፈገግታው ምድር የሚያሞቅ
ጨዋታው ሀዘን ሚያርቅ
ያ ሞገሱ ሞልቶ የሚታይ ለቀዬው ድምቀት የሆነ
ልጅሽ አንገቱን ደፍቷል ያስባል እንደመከነ

ህመሙን እንዴት ፤ልንገርሽ
መጥፋቱን እንዴት ላስረዳሽ
አታውቂማ አንቺ ተሰደሽ
ህዝብሽን ባለበት ትተሸ
ወደሌላው እየተጓዝሽ ከመንገድ ጠፍተሽ አታውቂም
የስደት ውሉ፤ ስሜቱ ሀገሬ አንቺ አይገባሽም
…. ከህዝብሽ እርቀሽ ሄደሽ ‘’አወይ የህዝቤ ሆታ
የባህል ጭፈራው ዝላዩና እስክስታ’’
ብለሽ ናፍቀሽ ታውቂያለሽ ?
አታውቂም!!  ስደት ላንቺ አይገባሽም
ተሰደሽ ስለማታውቂ ህመሙ አይሰማሽም!!
…ይህው ምስኪኑ ልጅሽ መንገድ መሪው
                                 ለቀዬው
መንገድ አስቶት ቆሟል
መሄጃው ግራ ገብቶታል
እናም አንቺ ሀገሬ ውጪና
ከህዝብሽ ተሰደጂና
የስደት ጠአሙን ቀምሰሽ
ልጆችሽን ሰብስቢና
መንገድ መሪው ልጅሽን
መንገድሽን አሳይውና
ሙቀትሽ የራቀው ሁሉ ከጉያሽ መሀል ገብቶ
አንገቱን ያቀረቀረም በኩራት ድምጡ አቅራርቶ
ሀገሬ ይበል በሀይሎጋ
የሁሉም ማማር አንቺው ጋ. ፡፡
                                                                                                                            ኤልያስ  ታ.                                                                                      03/08/2015  10:20 PM

አንድ ወንድሜ ከመንገድ ላይ መሄጃው ጠፍቶት ባጋጠመኝ ግዜ የተሰማኝ ስሜት ነው! ስንቱ በሰው ሀገር እንደጠፋ ቀርቷል!




!