Wednesday, August 5, 2015

ይድረስ ለጣይቱ



እኔ ነኝ ቦማርሌ
የጊታሬ ዜማ
ለዓለም የተሰማ
ፍቅር የሰበከ ሰላም የሰበከ
በመዋደድ ትግል ምርኮ የማረከ
እኔ ነኝ ቦማርሌ ለነፃነት ዜማ
ጊታሬ የሚሰማ፡፡
/////////////// 
አንቺ ነሽ ጣይቱ የነፃነት እናት
የክብር የሀገር የሰንደቅ እመቤት
የጦር ሜዳ መሪ
ጀግንነት ዘማሪ፡፡
////////////
ሰማሽ አንቺ ጣይቱ
ከሀበሻው ቀዬ ከእምብረቱ
እጄን ከፍ ያረኩቱ
እኔ ቦማርሌ ባንቺ ሀገር
እደመጣለው ስናገር፡፡
ከዛ ሆኖ እዚ ማዶ የጊታር ዜማን የሰማ
ያንቺው ህዝብ በኔ ተስማማ
የሰላም ዜማን አድምጦ ጊታሬ ልቡን ቢገዛው
በአክብሮት ሀውልት ያቆመ ሀበሻ እጅግ ለጋስ ነው
ሃበሻ እንዲህ ነው እንዴ
ነፃነቱን ለሰጠው ሳይሆን ስለ ነፃነት ላዜምኩ ለኔ
ለሀገሩ ለሞተ ሳይሆን ስለሀገሩ ላወራው ለኔ
ስንኙን የሚደረድር የሚያዜም መወድስ ቅኔ?
ጣይቱ ልሙትልሽ ሀበሻ አይከን አይወድም
የራሱን እየገደለ ለሌላ ነው የሚደክም
ለነፃነቱ የደማሽለት ህዝብሽ ካንቺ አብልጦኝ
ይሆን ሆይ እኔን ሊዘክር በሀገርሽ ሀውልት የሰጠኝ?
//////////////
ከነጊታሬ በክብሬ One Love እያልኩ ሳዜመው
ከሸገር ከከተምሽበት ሀውልቴን ከፍ ያደረገው
ላንቺ ግን ቦታ ጠቦታል ሀበሻ ስፍራም የለውም
የለገሽውን ሸገር ላንቺ ሀውልት አላደለውም::
ሰማሽኝ አንቺ ጣይቱ እኔም ዜማዬን እለጥቃለው
የነጻነት ብርሀን ይብራ ነጻነት ይታይ እላለው
የሰላም ሰንደቅ ይውለብለብ የነፃነት ሀውልትም ይቁም
አይከን ላለው ህዝብ ምልክት የነፃነቱም ትርጉም
አንቺ ነሽ ኩራት እናቱ
የጠላት ውጋት የህዝብ እረፍቱ
አንቺ ነሽ ውበት ድምቀቱ
የሰላም የነፃነቱ
አርማው አንቺ ጣይቱ፡፡


         ኤልያስ ታ.

          07/22/2015

Sunday, August 2, 2015

ተቀዶ የጠፋ ገፅ

---------------------
ከትልቅ ዶሴ ላይ ታሪክ ያጓደለ
ከመሀል ተነስቶ ለንባብ ያልዋለ
ከጥራዝ ከዶሴው ተለይቶ ያለ
ብዙ ታሪክ አለ።
-------------
ብዙ አለ ብዙ ገፅ ያልታየ ተቀዶ
ያልተነበበ ሀሳብ የቀረ ተማዶ
በባይተዋር አለም የገባ ያለቦታው
ብዙ አለ ብዙ ገፅ የጠፋ ከዶሴው
--------------
የተነጠለ ገጽ እውቀት እንደማይሆን
                        ታሪክ እንደማይሆን
ያልተሟላ ዶሴም ሙሉ እንደማይሆን
                        ጎዶሎ እንደሚሆን
ልብ ያላልን እኛ
የአንድ ዶሴን ታሪክ
በገፅ በምዕራፍ በቁጥር ተካፍለን
ቁንፅል ሀሳብ ሆነን
ጉንጥል ገጾች ሆነን

አለን! ብዙ አለን ተቀደን የጠፋን
ሆድ ብሶን ባይተዋር ጉንጥል ገፅ የሆንን
----------------
በባይተዋር ኑሮ በደመቀ ቀለም ተፅፎ መዘንጋት
የአንድ ዶሴ ታሪክ አጉድሎ ከመጥፋት
ከገፅ ዶሴነት
ከሀሳብ ታሪክነት
መሆኑ ባልከፋ
በጎዶሎ ገጾች ታሪክም ባልጠፋ።


                                 Elias T.
                                 New york 07/11/2015