Friday, April 27, 2012

ለእኛ ሰፈር ልጆች


ለእኛ ሰፈር ልጆች 
እኛ ልጅ ሆነን ያደግን 
በአፈር ተጫውተን ውሀ የተራጨን 
በፍቅር ተቃቅፈን ሲያሻን የተቧቀስን 
እኛ የድሮቹ
የጥንት ልጆቹ
በተጫወትንበት ባደግንበት ሜዳ
እኛ እንቆጥራለን እድሜያችን ሲቀዳ
"እርጅና መጣና ድቅን አለ ፊቴ"

ይሄን አንዘፍናለን ቀርቶ እቴሜቴ
እረ ቅሽምና ነው…….
ምንም ሳንሰራ አገር ሳናቀና አገር ሳንለውጥ
ወይ መንግስት ሣንቀይር ዝም ብለን ስንመርጥ
ወይ እንደነትና ካገር ሳንሰደድ
ዶላር ሳናመጣ
……………. እርጅናችን ይምጣ ¿¿¿¿¿
ወይ እንደነትና በእንትን ተይዘን እስር ቤት ሳንገባ
አልያም ጎጆ ብለን ሚስት ሳናገባ 
ወይ እንደነ ጒዴ ከጠረፍ ለማለፍ 
በምናምን አርገን በእንትን በኩል ስናለፍ
ህይወታችን ሳያለፍ
…… ወጣትነት ብቻ
ጥንካሬ ብቻ ከእኛ እያለፈ 
የእርጅናችን ሰነድ ከግንባር አረፈ
እኛ አኮ የምር ቀሽም ነን
ወይ እንደነእንትኖች አመጽ አስነስተን መንግስትን ሳንመርቅ
ወይ ከሀገር ተሰደን ለልማቱ ሳንጠደቅ
አልያም እነዳንዳንዶች ጋዜጣ ላይ መጻፍ መንግስትን ማማረር
ምንም በማናውቀው ጣልቃ እየገባን ዝምብለን መናገር
ይህ ሁሉ ያልሆነልን 
እርጅናችን ብቻ ጮቤ ሚረግጥብን 
ምን አይነት ጉዶች ነን
……… በቃ ክፈትልኝ የጒዴ ይሻላል 
"
እርጅና መጣና ድቅን አለ ፊቴ"
እባክህ ጨርሰው አንተ ሰው በሞቴ!!!!!!!!!!
10/07/04
E.T

የፊቴን የጥርሴን የአፌን
ጨዋታ ይህን ብቻ አይተው
የሆዴን ያንጀቴን የልቤን ረግጠው
አለፉ ትተውኝ
ውስጤን ሳይረዱኝ!!!!!!!!!
                                         19/08/04

Thursday, April 26, 2012

እንደ ክርስቶስ/ Ende Kerestose


እንደ ክርስቶስ
ከዛ ቀራንዮ ጫፍ ጌታ ተሰቅሎ አይተናል
ምክንያቱም ፍቅር ነው ብሎ ነግሮናል
ፍቅሬ ሆይ -
ይኸው እኔም በህይወት መስቀል ላይ ተሰቅያለው ተወጥሬ
ሁለት ሀሳቦች ይዘውኝ ከግራ ቀኝ ታስሬ
ሁለት ሀሳብ ይፈጀኛል
አንዱ  ሲለኝ ልቀቃት
ሌላው አይሆንም እሷ ያንተ ናት
እንዲ ነው የምወዛገብ እንዲ ነው ግራ እምጋባ
ከቀራንዮ ፍቅር ላይ አፈሳለውኝ ደም እንባ
ዙሪያሽ ያሉ የአንቺዎችሽ
ከኔ ይልቅ ገንዘብ ውበቱ የሆነ
ሁሉ በደጁ ሞልቶ በሀብቱ ዝና የገነነ
የርሱ ያረግሽ ዘንድ ይሻሉ
በአንድ ዳስ ውስጥ ስትኖሩ ይህን ሁሉ ይመኛሉ
እኔን ቤሳቤስቲንም የሌለኝ ምስኪኑን ያንቼ አፍቃሪ
እንዳይሽም አይፈቅዱኝም እንኳን ከኔ ልትኖሪ
ታድያ እኔም አንዳንዴ
የፍቅር ይሁን የንዴት መላውን በውል ሣላውቀው
ምናለ ይዟት በሄደ ባገባት ብዬ እመኛለው
ከኔ ጋር ችግር ጠፍንጓት ውበቷ ጠፍቶባት ከማይ
የደላው ይህ ሰውነቷ ጠይሞ በሀሩር ፀሀይ
ችግር ሲያቆሳቁላት ይህንንስ በዓይኔ ከማይ

ይውሰዳት እላለው መጥቶ
ከኔ ነጥሎ ለይቶ፡፡
አንዳንዴ
“የሰርግሽ እለት ጥሪው ደርሶኛል” እያልኩ ማዜም አስባለው
ሳልጠላሽ በውስጤ አርጌሽ ካደችኝ ባልኩኝ እላለው
ግን ይህም አይሆንም እንደማታረጊው አምናለው
ደግሞ አንዳንዴ ንፁ ፍቅራችን ድቅን እያለ ፊቴ
ያሳለፍነው የፍቅር ህይወት አልወጣ ብሎ ከአንጀቴ
ትውስ ይለኛል ሁሉም
በባዶ ኪስ ሀገር ለቀን በፍቅር የጠፋንበት
ነፍሳችን አለምን ገዝታ አንቺ የፍቅር ንግስት
                        እኔ ንጉሰ ነገስት
የሆንበት ዘመን ያጀግነኛል መልሶ
እንዴት ፍቅሬን ልነጠቅ አይወስዳትም ከኔስ ደርሶ
እላለው ባዶ በሆነ ኪሴ ከልቤ ፍቅርን ሞልቼ
አንቺ የኔብቻ ነሽ አትሄጂም ገንዘብ አጥቼ
እላለው፡፡
ይኸው በሕይወት ዓለም ላይ ግራ ቀኝ ተወጥሪያለው
ይህን ላንቺ አስባለው
ፍቅሬ እስቲ ይህን መልሺ
      ገንዘቡ መውድድ ይሆናል?
      ሀብቱ ሀሴት ይሰጣል??
      ፍቅሬስ መብል ይሆናል???
      መውደዴስ ከመታረዝ ያድንሻል????

እኔ ይህን አልመልስም
አንቺን ስለምወድሽ ችግርሽን ማየት አልወድም፡፡
ፍቅር ይሄ ከሆነ መውደድ ከራስ አብልጦ
እውነትን በሻሩ መሀል መሰቀል ለአይን ተጠልቶ
ይኸው ተሰቅያለው ክርስቶስን አይቼ
ገንዘብን በወደዱ በወዳጆችሽ ተጠልቼ
ግን እንደክርስቶስ መሆኑ ሳይቻለኝ ፍፁምነት
እነሆ ልጅሽ እንዳለው እነሆ ባልሽ ለማለት
አልቻልኩም ለዛ ባለሀብት
ፀሀይም አልጨለመችም
ጨረቃም ደም አልሆነችም
ብቻ ግን ይኸው አለውኝ ከግራ ቀኝ ተወጥሬ
ክርስቶስን እያየውኝ ስለ ፍቅር ስል ታስሬ
አባት ሆይ ያደርጉትን አላውቁም ልቦናቸው ሳይረዳ
ወይ ለነሱ ልቦና ስጣቸው ከንዋይ ሀሳብ የፀዳ
ወይ ለኔ ገንዘብ ስጠኝ
መውደዴን ይሁን እንዲሉኝ!!!!!!!!!!!!!!
                               
                                 
                                10/08/04