Thursday, July 9, 2015

የከረረ ክራር

የከረረ ክራር
ታም…. ታራራራም…. ታራራም
ታራራራራም
ራምራምራም 
እራምራምራም
ይላል ያስናቁ ክራር
ጣቶቿ ጅማቱን ሲያከር
ስትገርፈው ቅኝት ቀይራ
ይላል ታራራራራራራራም ታራራም
አላወቀች እሷትዝታን ስትቃኝ
ክራሯን ስትገርፈው
አንጀቴን በጣቷ እንደነዘረችው
በትዝታ ይዛ ከዚ እዛ ማዶ እንዳሻገረችው
ታምራራራራም ራራም ራም እያለ ወደዛ
ከፍቅሬ መዓዛ
ከእቅፉ በታች ከመውደዷ ጋራ
ልቤን በልቧ አስራ
ትለኛለች ውዴ
            ውዴ የኔ ፍቅር
ከጎንክ እንደዋልኩ ከእቅፍህ ልደር?
ትለኛለች ነፍሴ
የሌት መወድሴ
የቀን መናፈቄ
በአስናቁ ክራር ተስላ ከፊቴ
ታምታራም ታራራም ታራራም ታረረረረም ራም ራምራምምም
የሚገረፍ ክራር የሚያለቅስ አንጀት
አንቺን ያሰበ ለት
ታራራም እያለ ትዝታሽን ይዞ
የተጕዝነው ጉዞ
በፍቅርሽ በናፍቆት የሰለለ ልቤ
እያለ ሚያዜም የሌት ቀን ርሀቤ
ዜማውን ያወርዳል ተቀበይ ትዝታ
የአስናቁን ክራር የአደመጥሽው ለታ
ርም ርም ርምርምርምርም
ማራኪ ፈገግታሽ ይኸው ፊቴ ግጥም
እኔ ደግሞ ግጥም ሥገጥም ሥገጥም
የሰማች አስናቁ ክራሯን አነሳች
ዜማዋን ለጠቀች
“አልሻም ማስንቆን የፈረስ ጭራ ነው
አልሻም ዋሽንትን ወንዝ ዳር በቃይ ነው
አምጡልኝ ክራሬን አንጀትን በአንጀት ነው”
አለች ክራሯን ገረፈች
አንጀቴን ገረፈች
አንቺን የናፈቀ ነፍሴን እህ አስባለች
ክራሩ ከረረ ናፍቆቴ ከረረ
ይህንን የሰማ ክራር ተናገረ
አንቺን የናፈቀ
በናፍቆት አለቀ፡፡
                        ኤልያስ ታ.
                        06/25/2015

No comments:

Post a Comment