አቤቱ
የሆነብኝን አስብ
በጲላጦስ ፍርድ ላይ በሀሰት ስትወነጀል
ጀርባክ በጅራፍ ደምቶ ጉልበትክ በዳገት ሲዝል
አብራክ እንደደማችው በሀዘን ውስጧ ተሰብሮ
እንደ አዛኝቷ እናትክ ሀዘኗ ለሆነክ አብሮ
እነደሷ እኔም አነባው ልቤ በሀዘን ደማ
የምናገረው ላይኖረኝ ልጄ በሞት ተቀማ
… አቤቱ የሆነብኝን አስብ…
የሚፈስ ጣሪያዬን ሊደፍን ከእቅፌ እርቆ የሄደ
ምስኪኑ ያብራኬ ክፋይ በረሀ ገብቶ ወደቀ
ማተቡን እንዳጠበቀ…
… እጆችክ ከመስቀል ጋራ በምስማር ሲቸነከሩ
አካል በደም ተሞልቶ አጥንቶች ሲቆጠሩ
በእንባ የተሞላችው አንጀቷ ችሎ ያልቻለው
እናትክ ስንቱን አየችው
እኔም ምስኪኑ ልጄ እቅፌን ገና ያልጠገበው
አንገቱ በካራ ስለት ሲታረድ እንዴት ልቻለው
መሶቤን ሙሉ ሊያደርግ በረሀ ገብቶ የቀረ
ለኔ ሊያሳልፍ ሲጥር ባንገቱ ካራ አለፈ
እንዴት ልቻለው ከቶ የልጄን መታረድ ባይኔ
የደሙን መፈሰስ እያየው ጠፈብኝ የለቅሶ ወኔ
ልጄ ክብሬ ማረጌ የአይኔ ማረፊያ ሀብቴ
ስቅታው የሚያባንነኝ ተቀላ ይህው ከፊቴ
… አቤቱ የሆነብኝን አስብ …
ልጄ ስልጣን የለውም ሞትን ድል አርጎ አይመጣም
ዳግም ከእቅፌ ሆኖ እናቴ እነሆኝ አይልም
ታድያ ለዚ ምስኪን ደም ባህሩን ቀይ ላረገ
ሀሳቡን ከጫፍ ሳያደርስ በእንጭጩ ለጠወለገ
ምላሽክ አይዘግይ ጌታ ሆይ.. የፍርድህን ቀን አቅርብ
አቤቱ እለምናለው የሆነብኝን አስብ፡፡
በሊቢያ በረሀ አርገው ወደ ፈጣሪያቸው ላቀኑ ሰማህታት።
በሊቢያ በረሀ አርገው ወደ ፈጣሪያቸው ላቀኑ ሰማህታት።
ኤ..ታ 04/22/2015
No comments:
Post a Comment