Thursday, April 26, 2012

እንደ ክርስቶስ/ Ende Kerestose


እንደ ክርስቶስ
ከዛ ቀራንዮ ጫፍ ጌታ ተሰቅሎ አይተናል
ምክንያቱም ፍቅር ነው ብሎ ነግሮናል
ፍቅሬ ሆይ -
ይኸው እኔም በህይወት መስቀል ላይ ተሰቅያለው ተወጥሬ
ሁለት ሀሳቦች ይዘውኝ ከግራ ቀኝ ታስሬ
ሁለት ሀሳብ ይፈጀኛል
አንዱ  ሲለኝ ልቀቃት
ሌላው አይሆንም እሷ ያንተ ናት
እንዲ ነው የምወዛገብ እንዲ ነው ግራ እምጋባ
ከቀራንዮ ፍቅር ላይ አፈሳለውኝ ደም እንባ
ዙሪያሽ ያሉ የአንቺዎችሽ
ከኔ ይልቅ ገንዘብ ውበቱ የሆነ
ሁሉ በደጁ ሞልቶ በሀብቱ ዝና የገነነ
የርሱ ያረግሽ ዘንድ ይሻሉ
በአንድ ዳስ ውስጥ ስትኖሩ ይህን ሁሉ ይመኛሉ
እኔን ቤሳቤስቲንም የሌለኝ ምስኪኑን ያንቼ አፍቃሪ
እንዳይሽም አይፈቅዱኝም እንኳን ከኔ ልትኖሪ
ታድያ እኔም አንዳንዴ
የፍቅር ይሁን የንዴት መላውን በውል ሣላውቀው
ምናለ ይዟት በሄደ ባገባት ብዬ እመኛለው
ከኔ ጋር ችግር ጠፍንጓት ውበቷ ጠፍቶባት ከማይ
የደላው ይህ ሰውነቷ ጠይሞ በሀሩር ፀሀይ
ችግር ሲያቆሳቁላት ይህንንስ በዓይኔ ከማይ

ይውሰዳት እላለው መጥቶ
ከኔ ነጥሎ ለይቶ፡፡
አንዳንዴ
“የሰርግሽ እለት ጥሪው ደርሶኛል” እያልኩ ማዜም አስባለው
ሳልጠላሽ በውስጤ አርጌሽ ካደችኝ ባልኩኝ እላለው
ግን ይህም አይሆንም እንደማታረጊው አምናለው
ደግሞ አንዳንዴ ንፁ ፍቅራችን ድቅን እያለ ፊቴ
ያሳለፍነው የፍቅር ህይወት አልወጣ ብሎ ከአንጀቴ
ትውስ ይለኛል ሁሉም
በባዶ ኪስ ሀገር ለቀን በፍቅር የጠፋንበት
ነፍሳችን አለምን ገዝታ አንቺ የፍቅር ንግስት
                        እኔ ንጉሰ ነገስት
የሆንበት ዘመን ያጀግነኛል መልሶ
እንዴት ፍቅሬን ልነጠቅ አይወስዳትም ከኔስ ደርሶ
እላለው ባዶ በሆነ ኪሴ ከልቤ ፍቅርን ሞልቼ
አንቺ የኔብቻ ነሽ አትሄጂም ገንዘብ አጥቼ
እላለው፡፡
ይኸው በሕይወት ዓለም ላይ ግራ ቀኝ ተወጥሪያለው
ይህን ላንቺ አስባለው
ፍቅሬ እስቲ ይህን መልሺ
      ገንዘቡ መውድድ ይሆናል?
      ሀብቱ ሀሴት ይሰጣል??
      ፍቅሬስ መብል ይሆናል???
      መውደዴስ ከመታረዝ ያድንሻል????

እኔ ይህን አልመልስም
አንቺን ስለምወድሽ ችግርሽን ማየት አልወድም፡፡
ፍቅር ይሄ ከሆነ መውደድ ከራስ አብልጦ
እውነትን በሻሩ መሀል መሰቀል ለአይን ተጠልቶ
ይኸው ተሰቅያለው ክርስቶስን አይቼ
ገንዘብን በወደዱ በወዳጆችሽ ተጠልቼ
ግን እንደክርስቶስ መሆኑ ሳይቻለኝ ፍፁምነት
እነሆ ልጅሽ እንዳለው እነሆ ባልሽ ለማለት
አልቻልኩም ለዛ ባለሀብት
ፀሀይም አልጨለመችም
ጨረቃም ደም አልሆነችም
ብቻ ግን ይኸው አለውኝ ከግራ ቀኝ ተወጥሬ
ክርስቶስን እያየውኝ ስለ ፍቅር ስል ታስሬ
አባት ሆይ ያደርጉትን አላውቁም ልቦናቸው ሳይረዳ
ወይ ለነሱ ልቦና ስጣቸው ከንዋይ ሀሳብ የፀዳ
ወይ ለኔ ገንዘብ ስጠኝ
መውደዴን ይሁን እንዲሉኝ!!!!!!!!!!!!!!
                               
                                 
                                10/08/04



No comments:

Post a Comment