እኔ ነኝ ቦማርሌ
የጊታሬ ዜማ
ለዓለም የተሰማ
ፍቅር የሰበከ ሰላም የሰበከ
በመዋደድ ትግል ምርኮ የማረከ
እኔ ነኝ ቦማርሌ ለነፃነት ዜማ
ጊታሬ የሚሰማ፡፡
///////////////
አንቺ ነሽ ጣይቱ የነፃነት እናት
የክብር የሀገር የሰንደቅ እመቤት
የጦር ሜዳ መሪ
ጀግንነት ዘማሪ፡፡
////////////
ሰማሽ አንቺ ጣይቱ
ከሀበሻው ቀዬ ከእምብረቱ
እጄን ከፍ ያረኩቱ
እኔ ቦማርሌ ባንቺ ሀገር
እደመጣለው ስናገር፡፡
ከዛ ሆኖ እዚ ማዶ የጊታር ዜማን የሰማ
ያንቺው ህዝብ በኔ ተስማማ
የሰላም ዜማን አድምጦ ጊታሬ ልቡን ቢገዛው
በአክብሮት ሀውልት ያቆመ ሀበሻ እጅግ ለጋስ ነው
ሃበሻ እንዲህ ነው እንዴ
ነፃነቱን ለሰጠው ሳይሆን ስለ ነፃነት ላዜምኩ ለኔ
ለሀገሩ ለሞተ ሳይሆን ስለሀገሩ ላወራው ለኔ
ስንኙን የሚደረድር የሚያዜም መወድስ ቅኔ?
ጣይቱ ልሙትልሽ ሀበሻ አይከን አይወድም
የራሱን እየገደለ ለሌላ ነው የሚደክም
ለነፃነቱ የደማሽለት ህዝብሽ ካንቺ አብልጦኝ
ይሆን ሆይ እኔን ሊዘክር በሀገርሽ ሀውልት የሰጠኝ?
//////////////
ከነጊታሬ በክብሬ One Love እያልኩ ሳዜመው
ከሸገር ከከተምሽበት ሀውልቴን ከፍ ያደረገው
ላንቺ ግን ቦታ ጠቦታል ሀበሻ ስፍራም የለውም
የለገሽውን ሸገር ላንቺ ሀውልት አላደለውም::
ሰማሽኝ አንቺ ጣይቱ እኔም ዜማዬን እለጥቃለው
የነጻነት ብርሀን ይብራ ነጻነት ይታይ እላለው
የሰላም ሰንደቅ ይውለብለብ የነፃነት ሀውልትም ይቁም
አይከን ላለው ህዝብ ምልክት የነፃነቱም ትርጉም
አንቺ ነሽ ኩራት እናቱ
የጠላት ውጋት የህዝብ እረፍቱ
አንቺ ነሽ ውበት ድምቀቱ
የሰላም የነፃነቱ
አርማው አንቺ ጣይቱ፡፡
ኤልያስ
ታ.
07/22/2015


No comments:
Post a Comment